News | ዜናዎች | Oduu
የአፍሪካ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ማዕከል ከሁለት ድርጅቶች እና አራት የክልል ጤናና ትምህርት ቢሮዎች ጋር የሶስትዮሽ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ
የአፍሪካ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ማዕከል ከፓዝ ኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያ ስኩል ሬዲነስ ኢኒሽየቲቭ ጋር በመሆን የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች እና የቅድመ-አንደኛ መምህራንና ሱፐርቫይዘሮቻቸውን የአቅም ግንባታ ሥልጠና መርሃ ግብርን በይፋ ለመጀመር የሶስትዮሽ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
ይህ የስምምነት ማዕቀፍ የሕፃናትን ሁለንተናዊ ዕድገት እውን ለማድረግ ወሳኝ ምዕራፍ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ስኩል ሬዲነስ ኢኒሽየቲቭ ለትምህርት ዘርፉ ትግበራ ከየክልሎቹ የትምህርት ቢሮዎች ጋር በመተባበር አስፈፃሚነቱን ሲወስድ፣ ፓዝ ኢትዮጵያ ደግሞ በጤናው ዘርፍ በተመሳሳይ ከየክልሎቹ ጤና ቢሮዎች ጋር በመተባበር የቴክኒክ አስፈፃሚ ይሆናል።
የአፍሪካ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ማዕከል አጠቃላይ የትግበራ ቅንጅት ስራዎችን ያስተባብራል። በተጨማሪም የአማራ፣ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ የኦሮሚያ እና የሲዳማ ክልል የትምህርትና የጤና ቢሮዎች በዚህ መርሃ ግብር ውስጥ ዋና ፈፃሚ የመንግሥት አካላት በመሆን በንቃት ይሳተፋሉ።
በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ የአፍሪካ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ማዕከል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ከበደ ወርቁ፣ የኢትዮጵያ ስኩል ሬዲነስ ኢኒሽየቲቭ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ምኒልክ ደስታ እና የፓዝ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ናስር አሊ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል። በቀዳማይ ልጅነት ልማት ሥራዎች ላይ ሁንተናዊ የጤና አገልግሎቶችን በቅንጅት መስጠት እንዲሁም የቅድመ-አንደኛ ትምህርትን ጨዋታን መሠረት ያደረገ የማስተማሪያ ስነ-ዘዴን ተግባራዊ ማድረግ ለቀዳማይ ልጅነት ልማት የሚኖረው የላቀ ፋይዳ በመድረኩ ላይ ተነስቶ በስፋት ውይይት ተደርጎበታል።
ለዚህ ትልቅ ሀገራዊ ውጥን እውን መሆን የገንዘብ ድጋፍ ላደረገው የቪቶል ፋውንዴሽን በመድረኩ ምስጋና ተሰጥቶ፣በጉባኤው ላይ ለተገኙ የትምህርት እና ጤና ሚኒስቴር ተወካዮች፣የክልል መንግሥታት የትምህርትና ጤና ቢሮ አመራሮች፣ ከቴክኒክ አስፈፃሚ ድርጅቶች እና ሌሎች ቁልፍ ሚና ያላቸው አጋሮችም ለቀዳማይ ልጅነት ልማት የሚመደቡ ሀብቶች የነገውን ትውልድ ዕጣ ፋንታ የሚወስኑ በመሆናቸው፣ የተገኘውን ሀብት በከፍተኛ ኃላፊነትና ውጤታማ በሆነ ስልት መጠቀም እንደሚገባቸው በከፍተኛ አጽንዖት መሳሰቢያ ተሰጥቷል።